ተሾመ ዳባ
ምርጫ በአንባገነን መንግስት ውስጥ?
ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ የሚሆነው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተወዳዳሪ (free, fair and contested) ባህሪያትን የተላበሰ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ በኢ-ዴሞክራሲዊ መንግስት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች በምንም መመዘኛ የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች አይሆኑም፡፡ በሀገራችን በአጼው፣ በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመነ-መንግስታት ተደርገው የነበሩ ምርጫዎች የአጼውን፣ የደርጉንና የኢህአዴግን የአገዛዝ ስርዓቶች የስልጣን ዘመን ለማራዛም የተደረጉ (“mechanism of regime maintenance”) ምርጫዎች እንጂ አንዳቸውም የዴሞክራሲዊ ምርጫ ባህሪያትን የተላበሱ አይደሉም፡፡ በእርግጥ በባለፉት ሁለት የመንግስት ስርአቶችም ሆነ በኢህአዴግ ዘመነ-መንግስት የተደረጉ ምርጫዎች በተለያዩ የፖለቲካ አገዛዝ ስርአቶች ውስጥ እንደመደረጋቸውና በወቅቱ ካለው የሀገራችን የፖለቲካ ዕድገት አንጻር የተለያዩ ባህሪያትን የተላበሱ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በኢትዮጵያ ብቻ የታየ ሳይሆን በማንኛው ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስት ውስጥ የሚደረጉ ምርጫዎች አጠቃላይ ገጽታ ነው፡፡
