በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተዘረፈ ነው – ሚኒስትሩ
* ከ30 እስከ 40% የግንባታ ወጭ ይዘረፋል!!
የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሃይሌ ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሺን አጣሪ ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት ከመንገድ ስራ፣ ከባቡር መስመር ዝርጋታና፣ ከቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑን አምነዋል።
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ጥናት በባቡር መስመር ግንባታ 2.3 ኪሜ የባቡር ሃዲድ መስመር በሙስና ምክንያት ከደረጃ ውጭ እንዲሆን በመደረጉ የ124 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሷል። የአደጋ መከላከያ ብረቶች የተሰሩት ከወጣላቸው የጥራት ደረጃ በሶስት እጅ ያነሱ ሆነው በመገኘታቸው ጉዳዩ ለቦርድ ሰብሳቢው አርከበ እቁባይ ቢቀርብም ምላሽ ሳይሰጠው በመቅረቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የት እንደገባ ማወቅ አለመቻሉን ገልጿል።