Friday, February 20, 2015

ኢሕአዴግ የሕወሐትን የትግል ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ትግል ታሪክ አካል ለማድረግ መሥራት ይገባዋል! በኒቆዲሞስ

ጽሑፌን በአንድ ገጠመኜ ልጀምር፡፡ በአንድ ወቅት ከጎንደር አገር ገና በአፍላነት ወጣትነት ዘመኗ ወደ ትግል ከገባች ታጋይና ከእናቷ ጋር ለመገናኘትና በአንድ ምሽትም ውይይታቸውን ለማድመጥ ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ የትግል ዘመኑ በድል ተጠናቆ፣ አገር ተረጋግቶ በነበረበት ሰዓት ልጃቸውን ለመጠየቅና ለሕክምና ከጎንደር የመጡ እኚህ እናት በወታደራዊ ዩኒፎርምና ማዕረግ ተንቆጥቁጣ ከአጠገባቸው ተቀመጠችውን የትናንትናዋን የበረሃ ፋኖ የዛሬዋን ወታደራዊ መኮንን ልጃቸውን በዛች ቅጽበትም ልክ እንደ ልጅነቷ ዘመን ዓይን ዓይኗን በናፍቆትና በስስት እያይዋት እንዲህ አሏት፡-
እንደው ራቴዋ አሁንማ ሥልጣን ስትይዙ፣ ወንበሩም ሲደላደል፣ ምቾቱም ድሎቱም ሲመጣ እኮ ረሳችሁን … እንደው ያ ከእናንተ ከልጆቻችን ጋር ያየነው መከራና ሥቃይ፣ እንባችን፣ እግዚኦታችንና ጸሎታችን የሚረሳ ነው፡፡ ገና ጡቶችሽ እንኳን በቅጡ ሳያጎጠጉጡ ከአጎትሽ ልጅ ጋር ጠፍተሸ ወደ በረሃ ገባሽ የተባለበትን ዜና በሰማሁ እለት ያፈሰስኩትስ እንባ ልጄ፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ከሌሎች ታጋይ እህቶችሽና ወንድሞችሽ ጋር ወደቤት ተመልሰሽ ዓይንሽን በዓይኔ አይቼ በሕይወት መኖርሽን ባረጋገጥኩ ጊዜ መሬቱን ስንቴ ነበር በደስታ የሳምኩት፡፡ ትዝ አይልሽም…?!
የተንጨባረረው ጸጉርሽን፣ የገረጣው ፊትሽን ዓይቼ የልጅነት መልክሽና ውበትሽ እንዲያ ተለውጦ ሳይ የእናትነት አንጀቴ አላስችል ብሎኝ ምናለ ልጄ ወደቤትሽ ብትመለሽ ባልኩሽ ጊዜ አንቺና የበረሃ ጓደኞችሽ የሆናችሁ ታጋዮች በዛ በልጅነት ዘመናችሁ ወደ በረሃ የገባችሁበትንና የትግላችሁ ዓላማ ለነጻነት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት መሆኑን ደጋግማችሁ ስትነግሩንና ስታስተምሩን ውስጣችን ተረጋጋ፤ አይ ልጆቻችን ለዚህ ታላቅ ዓላማ ከሆነማ አባጃችሁ፣ እሰይ ኢትዮጵያ አምላክ ይከተላችሁ ብለን መርቀንና ለአገራችን ታቦት አደራ ሰጠናችሁ ነበር በደስታ ወደ ትግል የሰደድናችሁ፡፡
… ችግሩ፣ ራብና ጥሙ ሲጠናባችሁ በውድቅት ሌሊት ወደ እናቶቻችሁ ማጀት ስትመጡ ከራቡና ከጥሙ የተነሳ አንጀታችሁ ሰርጉዶ፣ ፊታችሁ ገርጥቶ ስናያችሁ የወላድ አንጀታችን እየተርገፈገፈ ነበር እንጀራውን አጥፈን ሲገኝ በወጥ፣ ሲታጣም በበርበሬ፣ ወተቱን፣ እርጎውንና ቅራሪውን እየሰጠናችሁ፣ በጎታውና በዋሻ እየደበቅናችሁ ነበር ያን ክፉ የመከራ ዘመን፣ ያን እንደ መርገ የከበደ የጭንቅ ቀን አብረን ያሳለፍነው፡፡
ልጄ እንደ እናንተ እንደ ልጆቻችን ነፍጥ አንግተን በርሃ ባንወርድም መከራችሁን መከራችን፣ ጭንቀታችሁን ጭንቀታችን፣ ብሶታችሁን ብሶታችን አድርግን አብረናችሁ ማስነናል፣ ደክመናል፣ በረሃ ለበረሃ፣ ዱር ለዱር ተንከራተናል፡፡ በዚህ የእናንተ የልጆቻችን ጭንቀትና አሳብ በሌላ በኩል የደርግ ወታደሮች ወንበዴዎችን እየደበቃችሁና እየቀለባችሁ የሚለው ክስና ወቀሳ ወከባና ማንገላታት እንዲያ ግራ ሲያጋባን፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ ያን የአንድ እናት አብራክ ክፋይ የሆኑ የወንድማማቾችን እልቂትና ደም መፋሰስ በቃ ይል ዘንድ የቀን ተሌሊት እግዚኦታችንን፣ ጩኸታችንን የአገራችን ታቦት ይመስክረዋ! ድካማችን፣ ልፋታችን፣ መውጣት መውረዳችን፣ አዎን ልጄ ላባችንና እንባችን ከእናንተና ከእልፍ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ደም፣ እንባና ላብ ጋር ተቀላቅሎ ከአገራችን አፈር ጋር በአንድነት ተላቁጧል- ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነጻነት፡፡
ያን ተስፋችን ከተስፋችሁ፣ ሕልማችሁ ከሕልማችሁ የተጋመደበትን በአንድ የተቋጠረበትን፣ ሞትን የሚተፉ ከላይ የእሳት ትንታግ፣ የእሳት አሎሎ የሚያወርዱት የአውሮፕላኖቹ ማጓራትና ውርጅብኝ፣ በምድር የሞት፣ የእልቂት እሳትን የሚተፉ፣ የሚያዘንቡ የከባድ መሳሪያው ፍንዳታና ጩኸት ያልበገረው፣ መከራው፣ ራብና ጥም የልፈታው፣ ሞት እንኳን ያላሸነፈውን፣ ያልረታውን የተሳስርንበትን ያን የጽኑ የነጻነትና የፍትሕ የቃል ኪዳን ውል የሚረሳ አንጀት ይኖራችሁ ይሆን ልጄ …?!
የነጻነት ፋኖዎች፣ ታጋዮች የሆኑ ይህን የእናትና ልጅ ትርክት፣ ክፉና መልካም ትዝታቸውን ሲያወጉ፣ ሲተርኩት መስማት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ እንዲሁም ሥቃይና መከራ ያልበገረውን የኢትዮጵያውያን እናቶች ጠንካራ መንፈሳቸውን፣ የወጣት ታጋይ ጀግኖችን ብርቱ ወኔያቸውን ጠንካራ ማንነታቸውን የሚከስት ነው፤ በአንጻሩም ደግሞ ውስጥን በኀዘን፣ በቁጭት የሚበረብር ነው፡፡
ለመሆኑስ በዚህች እናት ምድር ኢትዮጵያ ስንቶች ናቸው እንባቸውን፣ ላባቸውንና ደማቸውን ለአገራቸው ነጻነትና ልዑላዊነት፣ ለሕዝባቸው ፍትሕና እኩልነት ሲሉ የገበሩት፡፡ እነዛ የአፍላ ጉርምስና፣ የወጣትነት ምኞትና የስሜት ግለት ለአፍታ ሳያታልላቸውና ሳይበግራቸው፣ ከእናታቸው ጉያ፣ ከሞቀ ቤታቸው፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከሥራ ገበታቸው ተለይተው ‹‹ዱር ቤቴ ብለው›› የከተሙ የእዛ ፋኖ ትውልድ ኃያል ወኔና ጠንካራ መንፈስ፣ እልህ አስጨራሽ የተጋድሎ ታሪክ አልጋ በአልጋ የሆነ መንገድ ለሚያልም ለእኔ ትውልድ በሚገባ ሊነገርው፣ ሊተረክለት ይገባዋል፡፡
በእርግጥ የእኔ ብዕር በታጋይና በታጋይዋ እናት መካከል የነበረውን ውይይት፣ ወቀሳና ትዝታ በቃላት ኳኮሎ ከማቅረብ ባለፈ በእናትና በልጅ ልብና ዓይን ውስጥ በዛች ቅጽበት ይታይና ይመላለስ የነበረውን የደስታ፣ የኀዘን፣ የብሶት፣ የጭንቀት ስሜት በቃላት ለመግለጽ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ ያን እውነተኛ ስሜት ለመግለጽ፣ ምስሉን ለመከሰት ታሪኩ የአካል፣ የመሥዋዕትነቱ ተካፋይ መሆንን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ በእኚህ እናትና ታጋይ ልጃቸው ታሪካዊ ውይይት መነሻነት በዚህ ጽሑፌ የሕወሐትን ምስረታ 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሕዋሐት ታሪክና ጠቅለል ባለ መልኩም ደግሞ በታሪካችን ዙሪያ አንዳንድ አሳቦችን በማንሳት የውይይት አሳቦችን ለማጫር ወደድኹ፡፡
በአብዛኛው እኛ ኢትዮጵውያን ታሪካችንን በሚገባና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መዘገብ፣ መጻፍ፣ መናገርና ለቀጣዩ ትውልድ ሳይሸራረፍ እንዲሻገር፣ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ ገና ብዙ መሥራት ይቀረናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለታሪክ እውቀት ያለን ግንዛቤና ክብርም ዛሬ ዛሬ ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ እየመጣ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ በአንድ ወቅት የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ላጲስ ጌዴልቦ ‹‹የታሪክ ትምህርትና እውቀት የአገርና የኅብረተሰብ ግንባታ መሳሪያ ነው፡፡›› ብለው ነበር፡፡
በኢትዮጵያችን ምድር ግን ታሪክ ከአገርና ከኅብረተሰብ ግንባታ መሳሪያነት ጥቅም ከማዋል ይልቅ የጥፋት፣ የእልቂትና የበቀል ማወራረጃ መሳሪያ የመሆን ዕድሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ እየመጣ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ በአብዛኛው በእኛ አገር ታሪክ/ታሪካችንን የምንጽፍበትም ሆነ የምንተነተንበት መንገድ አድሎአዊነት የበዛበት፣ ፍትሐዊነት የጎደለው፣ ከእውነት ፈቅ ያለ በመሆኑ የጥላቻ፣ የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ የመጠላለፍ፣ የመናናቅና የወገንተኝነት መንፈስ በእጅጉ ያየለበት ነው፡፡
የአገራችን ታሪክ እንዲህ ውስብስብና የጥላቻና የጠብ መነሻ የሆነበትን ምክንያቶቹን በዚህች አጭር ጽሑፍ ለመዘርዘር፣ ለመተንተን የሚሞከር አይሆንም፡፡ ልሞክር ቢባልም ይህን ለማድረግ መዛግብትን ማገላበጥን፣ ጠለቅ ያለ ጥናት ማድረግን እንደሚጠይቅ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፡፡ አገራችን ያለፈችበትን ረጅም የታሪክ ዘመናት በቅጡ መፈተሽ፣ መመርመር፣ የኅብረተሰቡን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊና እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ መሠረት፣ ይህን ታላቅ ሕዝብ ለዚህን ያህል ዘመን በአንድነትም በልዩነትም፣ በፍቅርም በጠብም፣ በሰላምም በጦርነትም፣ በሃይማኖትና በባህል በአንድነት አስተሳስሮ ያቆየውን ጥልቅ የሆነ የሞራል መሠረትና ድንጋጌዎችን በጥልቀት ማወቅ፣ መመርመር፣ በቅጡ መረዳትም ያለብን ይመስለኛል፡፡
ከዚህም እውነታ ባሻገርም እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን በሚገባ መሰነድ፣ መመዝገብ ብቻ ሳይሆን ሌላው ዓለም በሚገባ እንዲያውቀው በማድረግና ወደ ገንዘብ ለመቀየር ጥበብና ብልሃት የጎደለንም መስሎ ይታየኛል፡፡ የኢሕዴግ መንግሥት ሕወሐት የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በቅርቡ ለአርቲስቶችና የጥበብ ሰዎች ባዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማ/ር ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በለጠ ታሪካችንን በመሰነድ፣ በመተረክና ሌላው ዓለም እንደሚያውቀው በማድረግ ረገድ ያጋጠማቸውን ትዝብት በቁጭት እንዲህ አካፍለውን ነበር፡፡
አቶ በለጠ ይህን የአፍሪካ ሕዝቦች የነጻነት ትግል ታሪክ አካል የሆነ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ደብቀን፣ ሸሽገን የተቀመጥን የታሪክ ስስታም ሕዝቦች መሆናችንን የወቀሱ አንድ ጋናዊ ፕ/ር ምሁር እንዳጋጠሟቸው ነበር በደደቢት በረሃ የጉብኝት ወቅት በቁጭት ሆነው ሲተርኩ የሰማናቸው፡፡
እርግጠኛ ነኝ የዛን ፋኖ ትውልድ የትግል ቆራጥ መንፈስና ጽኑ መንፈስ በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት የሰሙና ያዩ ሁሉ ሊሰማቸው የሚችለውን ስሜት ምን ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ በሰሜን ተራሮችና በረሃዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት፣ ለሕዝቦቿ ነጻነትና ክብር ከጉርአ እስከ ጉንደት፣ ከመተማ እስከ መቅደላ፣ ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ፣ ከደደቢት እስከ አሲምባ … ቀይ ባህርና ምጽዋ የፈሰሰው የአባቶቻችን፣ የእናቶቻችን ክቡር ደም መሥዋዕትነት ድምፅ ጎልቶ በሚሰማባቸው በእነዛ ሰሜን ተራሮችና በረሃዎች መገኘት ነጻነቱን ለሚያፈቅር፣ አገሩንና ወገኑን ለሚወድ ሕዝብ የሚሰጠው ትርጓሜ ልዩና በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነው፡፡
ሕወሐት ከአርባ ዓመት በፊት ከሰባት በማይበልጡና አሮጌ ነፍጥን ባነገቱ ወጣቶች እውን በሆነበት የደደቢት በረሃና የትግሉ እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ ክቡር ታሪክ በደም ተጻፈባቸው እነዛ የሰሜን ተራሮች፣ ዋሻዎች፣ ሸለቆዎች፣ በረሃዎች ውስጥ በአካል መገኘት፣ ከታሪኩ ባለቤቶች ዘንድ ምስክርነታቸውንና ትዝታቸውን ከአንደበታቸው መስማት ስሜትን የሚነዝር፣ የነጻነትን ክቡርነትና ታላቅነት የሚከስት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡
በእርግጥም በ50ዎቹ አጋማሽና በ60ዎቹ የሕዝባቸው ግፍና ጭቆና አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የተሰማቸው ወጣቶች ያቀጣጠሉት የትግል እሳት ለሕዝብ የገባውን ቃል/ተስፋ ከግቡ በማድረስ ረገድ ፈታኝ ጉዞው ላይ የተጋረጠው በእርስ በርስ እልቂቱና በደም የወየበው ታሪኩ የሚያሳፍር፣ የሚያሸማቅቅ ቢሆንም የዛ ቆራጥና ፋኖ ትውልድ የመከራ ናዳ ወኔውን ያላላላው፣ በጨካኞችና በአምባገነኖች የሞት ድግስ ፊት እንኳን ያልተበገረው ጽኑና ብርቱ መንፈሱ ግን መቼም ቢሆን ሊዘከር፣ ሊከበር የሚገባው ነው፡፡
ሕወሐትም ሆነ ኢሕአዴግ ይህን የኢትዮጵያ ሕዘቦች ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳይባል ትልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉበትን ታሪክ ወይም ታሪኩን በሚገባ ወደ ሕዝብ አድርሶታል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ኢሕአዴግ ለነጻነት ያደረገውን የተጋድሎ ታሪኩን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ አካል በማድረግ ረገድም ብዙም የተሳካ ሥራ ሠርቷል ብሎ ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እናም እነዛ ለነጻነት በፈሰሰ ክቡር ደም፣ መሥዋዕትነት ያሸበረቁ የሰሜን ተራሮች፣ በረሃዎች ነጻነትን ያበሰሩበት ኃያል ድምፃቸው እንደታፈነ፣ ያ ልዩ የሆነ የነጻነት ውበታቸው እንደተጋረደ ከትውልድ ተቆራርጠው ብቻቸውን እንዲቆዝሙ፣ እንዲብሰለሰሉ ተደርገዋል፡፡
ኢሕአዴግ ይህን ክቡር የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ከነሙላቱና ጉድለቱ በሚገባ መጻፍ፣ መተርክና ለጥቅም ማዋልም እምብዛም አልሆነለትም፡፡ ከዛ ይልቅ የታሪክ ሽሚያውና መቀራመቱ፣ ስስቱና የእርስ በርስ መከፋፋቱ አይሎብን አንድ አገር ሕዝቦች ታሪክ ለአንደኛው ወገን መኩሪያው፣ መፈከሪያው ሌላኛው ወገን ደግሞ ማፈሪያውና ማስፈራሪያ ሆኖ ታሪክ/ታሪካችን እርስ በርስ የምንሸናቋቆጥበት ወደመሆን አሳፋሪና አስፈሪ ወደሆነ ውርደትና ዝቅጠት እየወረድንበት መሆኑን ያየንባቸው እጅጉን ጎልተው የወጡባቸውን በርካታ አጋጣሚዎችን እያፈርንና እየተሸማቀቅን አይተናል፣ ታዝበናልም፡፡
በክቡር ታሪካችን የምንኮራውን ያህል ማፈር በሚገባን ታሪካችን እያፈርንና እየተቆጨን ዳግመኛ የደም፣ የበቀል ታሪክ እንዳይደገም በፍቅርና ዕርቅ መንፈስ አክመን፣ በእርስ በርስ በመነጋገርና በመግባባት በይቅርታ ዘግተን ወደሌላኛው የታሪክ ምዕራፍ እንሻገር ዘንድ መልካሙ አማራጭ፣ ትክክለኛው መንገድ ይኸው ይመስለኛል፡፡ እንደ አገርና ሕዝብ ለመኖር፣ ለመቀጠል ታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ለጲሶ ጌዴልቦ እንዳሉት፡- ‹‹ታሪክን የአገርና ኅብረተሰብ ግንባታ አካል አድረግን መቁጠር ይኖርብናል፡፡››
ስለሆነም በዚህ የታሪክ ሂደትና እውነታ ከተስማማን ወርኻ የካቲት በመጣ ቁጥር የሚዘከረው የሕወሐት ታሪክ እስከ ሙላቱና ጉድለቱም ቢሆን የኢትዮጵያችን/ሕዝባችን ታሪክ አካል እንደሆነ ነው የማስበው፣ የማምነው፡፡ ይህን ታሪካዊ እውነታ እውን በማድረግ ትናንትና እንደ አገርና ሕዝብ በደጉም በክፉው አስተሳስሮን የቆየው የታሪክ ሰንሰለት ሳይቋረጥ ለትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ የዚህ ታሪክ ዋንኛ ተዋናይ የሆኑት በሕይወት ያሉ የኢሕዴግ ታጋዮች ታሪካዊ ኃላፊነት ነው፡፡
ኢሕአዴግ ለሕወሐት የ40ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ከሚያደርገው ከሽር ጉዱና ከድግሱ ጋጋታ በበለጠ ክቡር ሕይወታቸውን ሳይሳሱ ለነጻነት የከፈሉ የሕዝብ ልጆች ታሪክ በሚገባ ይጻፍና ይተረክ ዘንድ ሊተጋና ሌሎችንም ሊያተጋ ይገባዋል፡፡ ኢሕአዴግ፣ መንግሥት የብዙ ሺዎች ጀግኖች፣ አባቶችና እናቶች ሕይወት መሥዋዕትነት የተከፈለበት ይህ ታሪክ የአገራችን፣ የሕዝባችን የረጅም ዘመናት የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ አካል ከመሆን ባለፈ በአፍሪካውያንና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን የሚያከብሩና የሚያፈቅሩ ሕዝቦች የትግል ታሪክ አካል እንዲሆን ከቃል ባለፈ በተግባር ጭምር ሠርቶ ሊያሳይ፣ ሊያረጋግጥ ይገባዋል፡

No comments:

Post a Comment